የ2015 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ሊቀ ጳጳስ እና ክቡር አምባሳደር ምሕረተ አብ ሙሉጌታ በተገኙበት በስቶክሆልም ከተማ በድምቀት ተከበረ !

(መስከረም 17 ቀን 2015 ዓ.ም ስቶክሆልም ፣ ስዊድን )

የ2015 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የስዊድን፣ ስካንድናቭያንና የግሪክ ሀገሮች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና በኖርዲክ ሀገሮች የኢፌዴሪ ልዩ መልእክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ምሕረተ አብ ሙሉጌታ በተገኙበት በስቶክሆልም ስዊድን በድምቀት ተከብሯል።

በዕለቱ ነገረ መስቀሉን የተመለከተ ሰፊ ትምህርተ ወንጌል በሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ በባህርዳር ከተማ የ፬ቱ ጉባዔያት መምህር ከመሰጠቱ በተጨማሪ በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እና በስቶክሆልም ከተማ የሚገኙት አራቱም አድባራት ሰ/ት/ቤት ወጣቶች ያሬዳዊ ዝማሬ ቀርቧል፣ መንፈሳዊ ትርዒቶችም ታይተዋል።

በመጨረሻም በብፁዕ አቡነ ኤልያስ የስዊድን፣ ስካንድናቭያንና የግሪክ ሀገሮች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ከተሰጠ በኃላ በብፁዕነታቸውና በክቡር አምባሰደሩ ደመራው ተለኩሷል ።

በደመራው በዓል ላይ ከሀገር ቤት በእንግድነት የተገኙትን ሊቀ ብርሃናት የኔታ ሐዋዝ ተበጀንና ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክን ጨምሮ የሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎች ፣ የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ የሰ/ት/ቤት አባላትና የከተማው በርካታ ምእመናን ተገኝተዋል።

በመ/ሥርዓት ቀሲስ ተስፋዬ ገደፋ
የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ

በፌስቡክ ያግኙን